Friday, September 16, 2016

ከ"በረሀ እሪያ የተላከ መልእክት"

                                            ከ"በረሀ እሪያ የተላከ መልእክት"

     አስልመዋል ተብለው የታሙት አቤቶ ኢያሱ የክርስትና ስማቸው "ክፍለ ያዕቆብ" እንደነበረ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ በ"ትዝታዬ፦ ስለራሴ የማስታውሰው" መጽሐፋቸው እንዳጫወቱን፤ እኔ ክፍሉ ሁሴን አህመድ ሁመድ አሊ አህመድም ስመ ጥምቀቴ "ክንፈ ገብርኤል" እንደነበር ያጫወትኮት አይመስለኝም።

    መቼም ምን ቁጡ ቢሆን በ"ነበር" ስላስቀመጥኩት ቁጡው ገብርኤል ቱግ የሚልብኝ አይመስለኝም። እኔ ራሴ ስም ጥምቀቴ ትክዝ የሚለኝ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋል እንዲሉ እንዲህ እንደ መርስዔ ኀዘን ወዝ ያለው ጫወታ የሚያመጣ ሲገኝ ነው።

    የጫወታ ነገር ሲነሳ መርስዔ ኀዘን ከላይ በጠቀስኩት መጽሐፋቸው ገጽ 136 ሌላ የሚያስደምም ነገር ያመጡና በእናቴ ወገን የነበሩት አያቴ መነኩሴ ነበሩ ብዬ ከዚህ ቀደም ያጫወትኮትን በሚከተለው አኳኃን ያስታወሱኛል።

    "አረጋዊ በምንኩስና የማዕረግ ተራ ከእንጦንስ ተጀምሮ ሲቆጠር በአራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ይኸውም እንደሚከተለው ነው። እንጦንስ ምንኩስናን ለመጀመሪያ ጊዜ መሠረተ። መቃርስ ከእንጦንስ የምንኩስናን ማዕረግ ተቀበለ። ጳኩሚስ ከመቃርስ የምንኩስናን ማዕረግ ተቀበለ። ቴዎድሮስ ሮማዊ ከጳኩሚስ የምንኩስናን ማዕረግ ተቀበለ። አረጋዊ ከቴዎድሮስ ሮማዊ የምንኩስናን ማዕረግ ተቀበለ።"
      እና በ1968 ዓ.ም ለአርባ ስድስት ዓመታት የኖሩበትን መቀሌን ትተው አዲስ አበባ እኛ ጋር መጥተው ከጥቂት ቀናት በኋላ ደብረ ሊባኖስ ሄደው መንኩሰው የተመለሱት አያቴ አቦይ ረዳ ገሠሠ ወቆ አባ ዳኮ በስንት ቢሊዮኖኛው የማዕረግ ተራ ያሉና ከማንስ ምንኩስናውን ተቀበሉት ይሆን? አሰኘኝ።


    ሆኖም በዛሬ ጊዜ ከበረሀ የመጡ "ነፃ አውጪዎች" አገሩን በጎሳ ሸንሽነውት፤ አገሬውንም በዘረኝነት በክለውት #ጎሰኝነትይለምልም በሚል ሀሽታግ አዲሱ (ድንቄም አዲስ!) ትውልድ በሚተጋተግበትና በዚሁ መጽሐፍ እንደተገለጸው (የተገለጸበት መንፈስ ሌላ ቢሆንም) ከ"በረሀ እሪያ በተላከ መልእክት" ተመስጦ፤ በጎሰኝነት እልህ አረፋ እየደፈቀ ያዙኝ ልቀቁኝ በሚልበት ሰዓት ማን እንደዚህ የመጣበትን ስር ከስር ጀምሮ በጥሞና እንዲመረምር የሚያደርግና ወደ ቀልቡ እንዲመለስ የሚያግዝ መጽሐፍ ያነሳል? ያው ከ"በረሀ እሪያ በተላከ መልእክት" መጠዛጠዝ ነውዪ!
 


አያቴና እኔ ቦሌ ሩዋንዳ ኤምባሲ በሚገኘው መኖሪያችን 1978


No comments:

Post a Comment